2 Samuel 17

1አኪጦፌልም፣ አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሰው መርጬ
ወይም፣ ልምረጥ
፣ በዛሬዪቱ ሌሊት አባትህን አሳድደዋለሁ፤
2በደከመውና ዐቅም ባነሰው ጊዜም አደጋ እጥልበታለሁ፤ ሽብር እለቅበታለሁ፤ ከዚያም አብሮት ያለው ሕዝብ ሁሉ ትቶት ይሸሻል፤ ንጉሡን ብቻ እመታዋለሁ፣ 3ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሳለሁ፣ አንተ የምትፈልገው የአንድ ሰው ብቻ መሞት ሁሉም እንዲመለሱ ያደርጋል። ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ በሰላም ይኖራል።” 4ምክሩም አቤሴሎምንና አብረውት የነበሩትን የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሁሉ ደስ አሰኘ።

5አቤሴሎም ግን፣ “እስቲ ደግሞ አርካዊውን ኩሲን ጥሩትና የሚለውን እንስማ” አለ። 6ኩሲ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ አቤሴሎም፣ “አኪጦፌል ይህን ምክር አቅርቧል፤ ታዲያ እርሱ ያለውን እናድርግ? ካልሆነም እስቲ የአንተን ሐሳብ ንገረን” አለው።

7ኩሲም አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “አኪጦፌል የሰጠው ምክር በዚህ ጊዜ የሚያዋጣ አይደለም፤ 8አባትህና ሰዎቹ የማይበገሩ ተዋጊዎችና ግልገሎቿ እንደ ተነጠቁባት የዱር ድብ አስፈሪ መሆናቸውን አንተም ታውቃለህ፤ በተጨማሪም አባትህ በቂ ልምድ ያለው ነው፤ ሌሊቱን ከሰራዊቱ ጋር አያድርም፤ 9እነሆ፤ አሁን እንኳ በአንዱ ዋሻ ወይም በሌላ ቦታ ተደብቆ ይሆናል። እርሱ ቀድሞ አደጋ በመጣል ከሰዎችህ ጥቂት ቢሞቱ
ወይም በመጀመሪያው ጥቃት አንዳንድ ሰዎች ቢወድቁ
ይህን የሰማ ሁሉ፣ ‘አቤሴሎምን የተከተለው ሰራዊት ዐለቀ’ ብሎ ያወራል።
10አባትህ ታላቅ ጦረኛ፣ አብረውት ያሉትም ጀግኖች መሆናቸውን እስራኤል ሁሉ ስለሚያውቅ፣ ልቡ እንደ አንበሳ ልብ ነው የተባለው ደፋሩ ወታደር እንኳ በፍርሀት ይርዳል።

11“እንግዲህ እኔ የምመክርህ ይህ ነው፤ ቍጥሩ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የበዛው፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለው እስራኤል ሁሉ ወደ አንተ ይሰብሰብና አንተው ራስህ ወደ ጦርነቱ ምራው፤ 12ከዚያም እርሱ የገባበት ቦታ ሁሉ ገብተን አደጋ እንጥልበታለን፤ ጤዛ በመሬት ላይ እንደሚወርድ እንወርድበታለን፤ እርሱም ሆነ ሰዎቹ አንድ እንኳ አይተርፉም፤ 13ከአንዲቱ ከተማ ቢገባ፣ እስራኤል ሁሉ ገመድ አምጥቶ አንድ ድንጋይ እንኳ እስከማይቀር ድረስ፣ ከተማዪቱን ወደ ሸለቆ ስበን እንከታታለን።”

14አቤሴሎምና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ፣ “ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የአርካዊው የኩሲ ምክር ይሻላል” አሉ፤ እግዚአብሔር በአቤሴሎም ላይ ጥፋት ለማምጣት ሲል መልካም የነበረው የአኪጦፌል ምክር ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጓልና።

15ኩሲም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን እንዲህ አላቸው፤ “አኪጦፌል አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው መክሯቸው ነበር፤ እኔ ግን እንዲህ እንዲህ አድርጉ ብዬ መክሬአቸዋለሁ። 16አሁንም በፍጥነት ላኩና፣ ‘በምድረ በዳው ባለው የወንዙ መሻገሪያ እንዳታድር፤ ሳትዘገይ ፈጥነህ መሻገር አለብህ፤ አለዚያ ግን ንጉሡና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ትዋጣላችሁ’ ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት።”

17በዚህ ጊዜ ዮናታንና አኪማአስ ወደ ከተማዪቱ ከገቡ ስለሚታዩ በዓይንሮጌል ይጠባበቁ ነበር፤ አንዲት ልጃገረድ አገልጋይ ወደዚያ እየሄደች በምትነግራቸው ጊዜ፣ እነርሱ ደግሞ ይህንኑ ወስደው ለንጉሥ ዳዊት ይነግሩት ነበር። 18ሆኖም አንድ ወጣት አያቸውና ለአቤሴሎም ነገረው፤ ስለዚህ ሁለቱም በፍጥነት ተነሥተው በብራቂም ወደሚገኝ ወደ አንድ ሰው ቤት ሄዱ፤ ሰውየው በግቢው ውስጥ ጕድጓድ ስለ ነበረው ወደዚያው ወረዱ። 19ሚስቱም በጕድጓዱ አፍ ላይ የስጥ ማስጫ ዘርግታ እህል አሰጣች፤ ማንም ይህን አላወቀም ነበር።

20የአቤሴሎም ሰዎች እዚያ ቤት ወደ ሴቲቱ ዘንድ መጥተው፣ “አኪማአስና ዮናታን የት አሉ?” ብለው ጠየቁ።

ሴቲቱም፣ “ወንዙን ተሻግረው ሄደዋል”
ወይም፣ በበጎች ጕረኖ አድርገው ወደ ውሃው ተሻገሩ
ብላ መለሰችላቸው፤ እነርሱም ፈልገው ስላጧቸው፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

21ሰዎቹ ከሄዱ በኋላ እነዚህ ሁለቱ ከጕድጓዱ ወጥተው ሄዱ፤ ለንጉሥ ዳዊትም፣ “አኪጦፌል በአንተ ላይ እንዲህ እንዲህ ብሎ ስለ መከረብህ ተነሥተህ በፍጥነት ወንዙን ተሻገር” አሉት። 22ስለዚህ ዳዊትና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ተነሥቶ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ሲነጋም ዮርዳኖስን ሳይሻገር የቀረ አንድም ሰው አልነበረም።

23አኪጦፌልም ምክሩን እንዳልተከተሉት ባየ ጊዜ፣ አህያውን ጭኖ ቤቱ ወደሚገኝበት ወደ መኖሪያ ከተማው ሄደ፤ ቤቱንም መልክ መልክ ካስያዘ በኋላ በገዛ እጁ ታንቆ ሞተ። በዚህ ሁኔታም ሞቶ በአባቱ መቃብር ተቀበረ።

24አቤሴሎም ከመላው የእስራኤል ሰዎች ጋር ዮርዳኖስን ሲሻገር፣ ዳዊት ግን መሃናይም ደርሶ ነበር። 25አቤሴሎምም በኢዮአብ ምትክ አሜሳይን በሰራዊቱ ላይ ሾመ፤ አሜሳይ የእስማኤላዊው
ዕብራይስጡና አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች፣ እስራኤላዊ ይላሉ፤ አብዛኞቹ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ግን፣ እስማኤላዊ ወይም ይዝራኢላዊ ይላሉ (1ዜና 2፥17 ይመ)።
የዮቴር ልጅ ነበረ፤ ዮቴርም የኢዮአብን እናት፣ የጽሩያን እኅት፣ የናዖስን ልጅ አቢግያን
በዕብራይስጥ፣ አቢግያ ማለትና አቢጋኤል ማለት አንድ ነው።
አግብቶ ነበር።
26እስራኤላውያንና አቤሴሎም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ።

27ዳዊት መሃናይም ሲደርስ፣ ከአሞናውያን ከተማ ከራባ የመጣው፣ የናዖስ ልጅ ሾቢ፣ ከሎዶባር የመጣው የዓሚኤል ልጅ ማኪርና ከሮግሊም የመጣው ገለዓዳዊው ቤርዜሊ 28መተኛ ምንጣፎች፣ ወጭቶችና የሸክላ ዕቃዎች ይዘው መጡ፤ እንዲሁም ስንዴና ገብስ፣ ዱቄትና የተጠበሰ እሸት፣ ባቄላና ምስር
አብዛኞቹ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞችና የሱርስቱ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ግን፣ ምስርና የተቈላ ባቄላ ይላል።
29ማር፣ እርጎ፣ በጎችና የላም አይብ እንዲበሉ ለዳዊትና ለሕዝቡ አመጡላቸው፤ ይህን ያደረጉትም፣ “ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቧል፤ ደክሟል፤ ተጠምቷል” በማለት ነው።

Copyright information for AmhNASV